ጃፓን ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ድጋፌን አጠናክራለው አለች

ሚያዝያ 4/2014 (ዋልታ) የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ፡፡

የጃፓን መንግሥት ለሰላም ህጻናት መንደር የጨርቃ ጨርቅ ማሰልጠኛ ማዕከል የማስፋፊያ ግንባታ የሚውል 49 ሺሕ ዶላር፣ 10 የስፌት ማሽንና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ድጋፉ ተቋሙ በርካታ ሰው ተቀብሎ ለማሰልጠን እንደሚያስችለው ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ የጃፓን መንግሥት ከ400 በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በመሥራት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዳደረገ ገልጸው በተለይም የጃፓን ልማት የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የበኩሉን እያደረገ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘገባ ያመለክታል፡፡

የሰላም ህጻናት መንደር የጨርቃ ጨርቅ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጫሊ ድጋፉ ተቋሙ በርካታ ሰው ተቀብሎ ለማሰልጠን ያስችለዋል ብለዋል፡፡

የተጠናቀቀው ይኸው የማስፋፊያ ግንባታም በዓመት 200 ተማሪዎች በተጨማሪ ለማሰልጠን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡