ገንዘባችንን፣ ዕውቀታችንንና ጉልበታችንን እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከማዋል በላይ ሀገርን የመውደድ መገለጫ የለም – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) ገንዘባችንን፣ ዕውቀታችንንና ጉልበታችንን እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከማዋል በላይ ሀገርን የመውደድ መገለጫ የለም ሲሉ ጠቀላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ፒኤችዲ) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም ጸንታ የቆመችው ለሌሎች በሚደረግ መልካም ነገር መሆኑንም በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡

ከለውጡ ወዲህ ከተከተልናቸው መርሖች አንዱ በማኅበራዊ ኃላፊነት ማኅበራዊ ችግሮችን መፍታት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ማዕድ ማጋራት፣ የድኾችን ቤት መሥራት፣ ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን መገንባት፣ የችግረኛ ገበሬዎችን እርሻ ማረስ፣ አካባቢን አረንጓዴ ማድረግ ባህል እንዲሆኑ ሠርተናል ብለዋል።

ሚልዮኖችም የዚህ ተሳታፊ ሆነዋል። ከሕጻናት እስከ አረጋውያን ባህላቸው አድርገውታል ሲሉም አክለዋል።

በዚህ ዓመት በተደረጉት እነዚህ ማኅበራዊ አገልግሎቶች የተሳተፋችሁትን ሁሉ በራሴና በመንግሥት ስም አመሰግናችኋለሁ ብለው አገልግሎቱን ያገኙት ወገኖች እንደሚመርቁንና እንደሚጸልዩለን አምናለሁም ብለዋል።

ኢትዮጵያችን በእነዚህ ወገኖች ምርቃትና ጸሎት ፈተናዎቿን አሸንፋ እንደምትጓዝ ርግጠኛ ነኝ በማለት መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።