ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ላይ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨታቸው ህዝብን እንደመናቅ የሚቆጠር መሆኑን ገለጸች

ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ

ኅዳር 11/2014 (ዋልታ) የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙኃን በህዝብ በተመረጠው መንግሥትና ኢትዮጵያ ላይ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨታቸው ህዝብን እንደመናቅ የሚቆጠር ድርጊት መሆኑን ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ገለጸች።

ኢትዮ አሜሪካዊት የሲቢኤስ ጋዜጠኛዋ ሔርሜላ አረጋዊ ዘ ሬይ ዞን ከተባለ የዜና ድረ-ገጽ ጋር ባደረገችው ቆይታ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ለኢትዮጵያ ቀርቶ ላለፉት በርካታ ዓመታት ላስተዳደረው የትግራይ ህዝብም እንደማይጠቅም በተግባር አሳይቷል ብላለች።

የሕወሓት ሽብር ቡድን “አዲስ አበባን ለመቆጣጠር እየተቃረበ ነው” የሚለው የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን የተለመደ በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ዘገባ እና ፕሮፖጋንዳ መሆኑንም አመልክታለች፡፡

የህዝብ ይሁንታን አግኝቶ በህግ የተመረጠን መንግሥት በሐሰተኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የመንግሥትና የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም የሚጎዱ ሐሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት ለህዝብ ክብር አለመስጠት መሆኑንም አንስታለች፡፡