ግድቡ ለአካባቢው ሃገራት የሚተርፍ ጥቅም አለው – አምባሳደር ነቢል መህዲ

ነሐሴ 10/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል መህዲ ከደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ዴንግ ዳው ጋር በወቅታዊና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡
በውይይቱ አምባሳደር ነቢል በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አተገባበር ዙሪያ ያሉ አዳዲስ ለውጦችን በተመለከተ ለምክትል ሚኒሰትሩ ገለጻ አድርገዋል።
የሁለትዮሽ ትብብሩን ከማጠናከር አንጻር ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ለ145 ደቡብ ሱዳናውያን ተማሪዎች ከሰጠችው ነጻ የትምህርት እድል በተጨማሪ በቀጣይ ሳምንት በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ስፔሻላይዝ የሚያደርጉ እጩዎች ምልመላ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ምክትል ሚኒስትሩ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች የምትሰጠው ነጻ የትምህርት እድል ሃገሪቱ ያለባትን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እያቃለለ መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ሃገራት የሚተርፍ ጥቅም እንዳለው በመግለጽ የሁለተኛ ዙር ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲደርስ እያደረገ ያለውን ጥረት አበረታች ነው ያሉት ዴንግ ዳው አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሚያወጧቸው ዘገባዎች ገንቢ ሚና ይኖራቸዋል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዳይወጣ አልፎ አልፎ እንቅፋት እንደሚገጥመው መንግሥት እንደሚያውቅ በመግለጽ ችግሩን ለመቅረፍ አስፈላጊው ማስተካከያ እንደሚደረግ ምክትል ሚኒስትሩ ቃል መግባታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡