ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጫካ ፕሮጀክት ስፍራ ችግኞችን ተከሉ

ሐምሌ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጫካ ፕሮጀክት ስፍራ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን ነው በጫካ ፕሮጀክት ሀገር በቀል የአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን ተከላ ያካሄዱት።

የባህር ዛፍን በሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች የመተካቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ “የምትተክል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የጀመርነውን የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ዛሬ በጫካ ፕሮጀክትም ቀጥለናል ብለዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ ግብር ከተጀመረ በኋላ የመሬት መራቆትን በመከላከል የተፈጥሮ ኃብትን መጠበቅና የደን ሽፋን እንዲጨምር አስችሏል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክረምቱን ችግኞችን በመትከል ለአረንጓዴ ምድር እንበረታለን ነው ያሉት፡፡