ጠቅላይ አቃቤ ህግ የጁንታው ቡድን የፈፀመውን ወንጀል የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ይፋ አደረገ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የጁንታው ቡድን ህግን በመጣስ ብሎም ሀገርን በመካድ የፈፀመውን ወንጀል የሚያሳይ የምርመራ ውጤት ይፋ አደረገ።

በመቐሌ፣ በማይካድራ እና በሌሎች አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብዓዊ ጥሰት፣ የፌዴራል መንግስትን አደጋ ላይ በመጣል እና ሀገርን በመካድ ወንጀል የተሰማሩ አካላትን ላለፉት 3 ወራት ግብረሀይል በማቋቋም ሲመረምር መቆየቱ ተነግሯል።

በዚህም 253 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች የነበሩ ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎቹ ጡረታ የወጡ እና ከፀጥታ ተቋማት ከድተው ሀገርን በማፍረስ በወንጀል የተሰማሩ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 96 የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበት ሲሆን፣ ህቡዕ የሆነ ፅንፈኛ ቡድን በማደራጀት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የፌዴራል ፓሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ም/ ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ሀገርን ለማመስ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በስልጣን ላይ የነበሩ እንዲሁም በጡረታ ላይ የነበሩ 349 ተጠርጣሪዎች የነበሩ ሲሆን፣ 124ቱ በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተቀሩት በህግ ማስከበር ሂደቱ መደምሰሳቸውን ተናግረዋል።

በዚህ የምርመራ ሂደት ከ680 በላይ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ በጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በቢሮዎች የተገኙ መረጃዎች ሀገርን ለማፍረስ መዘጋጀታቸውን እንደሚያሳይ ኮሚሽነር ዘላለም አመልክተዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅለይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ በበኩላቸው፣ ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ከተከሰተው ክስተት አስቀድሞ በበርካታ ሁነቶች ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበረ ገልፀው፣ ቡድኑ የትግራይ ማእከላዊ ኮሚቴ ኮማንድ የሚል መዋቅር በመዘርጋት በበጀት፣ በሰው ኃይል ስልጠና እና በመሳሪያ አቅርቦት ሲያደረጅ ነበር ብለዋል።

በዚህም ለአዲሱ መዋቅር ከ566 ሚልየን ብር በላይ የበጀተ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ በጀቱ 525 ሺህ ብቻ በአካውንቱ መገኘቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ መሰቦ ስሚንቶ፣ ሱር ኮንስትራክሽን እና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነርንግ ምሽግ በመቆፈር፣ መንገድ በመቁረጥ እንዲሁም የጦር መሳሪያ በማመላለስ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ተገልጿል።

የጁንታው ቡድን ለጦርነቱ ቀድሞ በመዘጋጀት ከ170 ሺህ ልዩ ኃይል በላይ በማዘጋጀት ጦርነት መጀመሩም ተገልጿል፡፡

ጦርነቱንም በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስቦ እና በቂ ፋይናንስ በጅቶ መግባቱንም በምርመራው መረጋገጡን አቶ ፍቃዱ አብራርተዋል፡፡

የማይካድራውን ጅምላ ጭፍጨፋ በተመለከተም በተሰጠው መግለጫ 256 ተጠርጣሪዎች ተሳታፊ እንደነበሩ እንደነበሩ እና ከተጠርጣሪ ወንጀለኞቹ መካከል 110 የሚደርሱ ሰዎች ሙሉ መረጃቸው የተጠናቀረ ሲሆን፣ 137ቱ በቁጥጥር ስር ውለው 37 የሚሆኑት በምስክሮች የተጠናቀረ ሙሉ ምርመራ ተካሂዶባቸዋል ተብሏል።

ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በተደረገ የተደራጀ ሳይንሳዊ የአስከሬን ምርመራ በቤተ ክርስቲያን 85 ጉድጓዶች፣ በመስጂድ 2 እንዲሁም በእርሻ ቦታዎች 24 እና በጅምላ የመቃብር ቦታዎች 6 ጉድጓዶች ተከፍተው ምርመራ መካሄጉ ተገልጿል።

በዚህም በጅምላ ጭፍጨፋ ወቅት የተገደሉ ወጣቶችን ለይቶ ለማወቅ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በወቅቱ ህይወታቸውን ያጡ የአማራ ተወላጅ ወጣቶች ቁጥር በውል የማይታወቅ መሆኑን የገለፁት ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ በማህበራዊ የትስስር ገፁ እንደሚናፈሰው ከፍተኛ ቁጥያ አለመሆኑን ገልፀዋል።

በመጨረሻም የምርመራ ሂደቱ ላለፉት ሶስት ወራት የህወሓት ቡድን አገርን ለማፍረስ ተደራጅቶ የሰራውን ወንጀል ብቻ የሚመረምር ግብረኃይል የተቋቋመ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ ምርመራው በቀጣይም የህወሀት ቡድን ላለፉት 27 አመታት የዘረፈውን ሀብት ለማስመለስ እንዲሁም ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

 

(በቁምነገር አህመድ)