ጠንካራ እና የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ

የካቲት 21/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ያማከለ ጠንካራ እና የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት መገንባት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።
ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች እየተሰጠ ያለው ሥልጠና ቀጥሏል፤ በዛሬ ውሎው “አገር በቀል ኢኮኖሚና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ” በሚል ርዕስ ገለፃ ተሰጥቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለአምባሳደሮች እንደገለፁት አሁን ያለው ዓለማዊ ሁኔታን በማጤን የአገራችን ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ዘርፈ ብዙ በሆነው የአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ሥርዓት በሥራ እድል ፈጠራ፣ በኢንቨስትመንት ፍሰት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና ዘላቂ የማኅበራዊ እድገት ሊያመጣ እንደሚያስችል የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በሥልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙት አምባሳደሮች ላነሷቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እንደተሰጠም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።