ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በጅማ ዞን የቡና እና በጋ የመስኖ ስንዴ ኩታ ገጠም እርሻዎች ምርት አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ገለጹ

የካቲት 5/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጅማ ዞን እና ከተማ ዙሪያ በመልማት ላይ የሚገኙ የቡና እና የበጋ የመስኖ ስንዴ ኩታ ገጠም እርሻዎች ምርት አበረታች ውጤት አስገኝቷል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአካባቢን ሥነ-ምኅዳር መሠረት ያደረጉ የሰብል ዓይነቶችን በስፋትና በጥራት እንዲመረቱ ማስቻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገባ ምርትን ለመተካት እና ገቢን ለማሣደግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በጅማ ዞን በበጋ መስኖ የለማ ስንዴ እንዲሁም የቡና ልማት ክላስተርን ጎብኝተዋል።