ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን አስጀመሩ

ግንቦት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።

የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ፕሮጀክቱ የአገራችንን አዲስ የፈጠራና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ልማት ጅማሮን የሚያበስር መሆኑን ገልጸው የኢኮኖሚ ፈጠራን በማራመድ፣ የአከባቢውን ማህበረሰብ በማብቃትና ዘላቂነትን በማረጋገጥ ረገድም ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ፈጠራን በማራመድ ረገድ ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ የማዕዘን ድንጋይ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ የወጪ ንግድ በማስፋፋትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት እንዲሁም የላቁ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎችን በማጎልበት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖረው ታስቦ የተነደፈ እንደሆነም አንስተዋል።

ስትራቴጅካዊ ትኩረቱን በላቁ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና በዘላቂ አሠራሮች ላይ በማድረግ፣ ዞኑ ለመላው አፍሪካ የኢኮኖሚ ዞኖች አዲስ ደረጃ ያስቀምጣልም ነው ያሉት።

መሠረቱን የመንግስት ርዕይ 2025 ያደረገው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክትነቱም በላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም መከበር ያለንን ቁርጠኝነት የሚወክል ነው ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አመላክተዋል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ በማብቃት ረገድ ኢኒሼቲቩ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስራዎችን ይፈጥራል፤ የሀገር ውስጥ የስራና የክህሎት እድገትን ያፋጥናል፤ በተጨማሪም የተጓዳኝ ኢንዱስትሪዎችን እድገት ያበረታታል ሲሉም አክለዋል፡፡

በውጤቱም ክልላዊ ልማታችንን ያፋጥናል፤ ለዘላቂነት ቁርጠኛ የሆነው ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን፣ የአካባቢን ተፅእኖ መቀነስ የሚያስችሉ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችንና ፈጠራዊ አሰራሮችን በማዋሃድ ለወዳጀ-ከባቢ የኢንዱስትሪ ልማት አዲስ ፈር መቅደድ እንደሚፈልግም ገልጸዋል፡፡

ለመጪው ጊዜ ብርሀን በሚፈነጥቀውና የብልጽግናን መሠረት በሚጥለው በዚህ የለውጥ ፕሮጀክት ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን በድጋፍና በተሳትፎ በመቀላቀል የታሪካዊው ጉዞ አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታው የተጀመረው በአዳማ እና ሞጆ ከተሞች መካከል በምትገኘው ሉሜ ወረዳ ነው።