ጠ/ሚ ዐቢይ “የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት ታሪክ” ዙሪያ የተካሄዱ የምርምር ውጤቶችን ተመለከቱ

ጥቅምት 14/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በእንጦጦ ፓርክ በሚገኘው የስነ-ጥበብ ማዕከል አማካኝነት “የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት ታሪክ” ዙሪያ የተካሄዱ የምርምር ውጤቶችን ተመለከቱ።

በማዕከሉ የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት ታሪክ፣ የኪነ-ህንፃ ጥበብ እና የአርኪዮሎጂያዊ የምርምር ትንተናዎችን የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በስነ-ጥበብ ማዕከሉ የቀረቡ የጥናትና ምርምር ስራዎች በኢትዮጵያ የእይታዊ ስነ-ጥበብ እድገት በጎ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

በተለይም ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ታሪካዊ ሀብቶች ተጠቅመው ዛሬ ላይ ሀገራቸውን እንዲገነቡ ትልቅ ተነሳሽነትን የሚፈጥር እይታዊ ስነ-ጥበብ ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ በመታገዝ በማዕከሉ መመልከታቸውን አንስተዋል።

በእንጦጦ የስነ-ጥበብ ማዕከል “ላሊበላ በእምነት የታነፀ” በሚል ሀሳብ በቴክኖሎጂ ታግዞ የቀረበው ዐውደ-ርዕይ በስፍራው በዓይን ሊታዩ የማይችሉ የላሊበላ ሀይማኖታዊና የኪነ-ህንፃ ጥበብቦች በማዕከሉ ውስጥ ለማየት የሚያስችል እንደሆነም ተጠቁሟል።

በደረሰ አማረ