ጦርነትን በመመከት የሲዳማ ህዝብ የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

ጥቅምት 29/2014 (ዋልታ) የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በሀገር ኅልውና ላይ የተከፈተውን ጦርነት በመመከት የሲዳማ ህዝብ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የሲዳማ ህዝብ አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔን የሚያወግዝ ሰልፍ በሀዋሳ ከተማ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ሕወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱን መዝረፉንና ህዝብን ላልተገባ እንግልት መዳረጉን አንስተዋል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት የጦር ዐውደ ውጊያውን በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ቢያደርግም የኢትዮጵያን ኅልውና በመፃረር መላውን ህዝባችንን የደፈረ ነው ማለታቸውን ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኅልውና ዘመቻው የኢትዮጵያ ህዝብን ይበልጥ አንድነቱን የሚያጠናክረው እንጂ የሚያዳክመው አይሆንም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጫፍ እስከጫፍ በመነሳት እየመከቱት ይገኛሉ ብለዋል።