ፈተናው ያለምንም ችግር በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች መጀመሩን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

ጥቅምት 8/2015 (ዋልታ) የ12ኛ ክፍል 2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ያለምንም ችግር በሁሉም የፈተና ጣቢያዎች በሰላም መጀመሩን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።

ፈተናው የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መርኃ ግብር መሠረት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ “ከመጀመሪያው ዙር ተምረን በርካታ ነገሮችን ስላስተካከልን የዚህ ዙር ፈተና በተጀመረበት መልኩ እንደሚጠናቀቅ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

የ12ኛ ክፍል የ2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መሠጠት የተጀመረ ሲሆን የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ፈተናውን በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው አስጀምረዋል።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ እንዲፈተኑ መደረጉ በትምህርት ሥርዓቱ ያለውን የሞራል ስብራት የሚጠግን መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህም ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው ማኅበረሰቡም በሚገባ የተረዳ እና የደገፈው በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን ብለዋል።

የ2ኛው ዙር ፈተና ከጅምሩ ምንም ችግር አላየንበትም ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣይ በፈተና ሥርዓቱ ያሉ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ቀርፈን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንገባለን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ እና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስፈተነ ይገኛል።

የ2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተና ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚሰጥ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW