ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ሆና የማይበገር ሠራዊት ገንብታለች አሉ

                                                     ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ጥር 26/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ሆና የማይበገር ሠራዊት መገንባት መቻሏን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለፁ።

የሠሜን ምዕራብ ዕዝ የሜዳይ እና የማዕረግ ሽልማት መርሃግብር በሁመራ ከተማ ያካሄደ ሲሆን በመርሀግብሩ ላይ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ሀገር በጦርነት ውስጥ ሆና የገነባችው ሠራዊት እጅግ አኩሪ እና ሀገሪቱ በሠራዊት ግንባታ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የላቀ ሞራል የሚያጎናፅፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው ሕወሓት የምዕራብ ኮሪደርን የማስከፈት ህልም ለማክሸፍ ሠራዊቱ በተጠንቀቅ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በመርሃግብሩ ለተሸላሚዎቹ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጠላት በሠሜን ምዕራብ በማድረግ በደብረዘቢጥና ጋሸና የተማመነበትን ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ ምሽግ በመደረማመስ የጠላትን ህልም ከማክሸፍ አልፎ ለዛሬ ሠላም ተጋድሎ ያደረገና ያሸነፈ ብርቱ ሠራዊት መሆኑን ገልፀዋል።

ሽልማቱም ለዚህ ተጋድሎና ድል ለማመስገን እና በዕዙ ብሎም በሠራዊቱ ውስጥ አርዓያነት በመፍጠር ለሀገር የሚከፈልን ዋጋ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ገልፀዋል።

ድሉ ሠራዊቱ ያለውን አቅም ሁሉ አደራጅቶና አቀናጅቶ ያገኘው ከመሆኑ በተጨማሪ በሕዝባዊ እና መንግሥታዊ ድጋፍ የክልል የፀጥታ መዋቅሮች በአንድነት ያስመዘገቡት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

“ሕወሓት ከለውጡ በኋላ 7 ክህደቶች ፈፅሟል፤ ለስምንተኛ ጊዜ ደግሞ በአፋርና አማራ ውጊያ ሲያስፋፋ በተሳሳተ የድጋፍ ግምገማ በመሆኑ ለዘጠነኛ ጊዜ እንዳይሳሳት እናስጠነቅቃለን” ብለዋል።

ሁሉም ዕዞች በሙሉ ዝግጁነት ጦርነቱን ለመጨረስ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሜዳያችሁ ለጀግኖች የተሠጠ በመሆኑ ለቤተሠብ የሚያኮራ ለተተኪ አርያነት እንዲኖረው በአግባቡ መያዝና ማስቀመጥ ይገባል ማለታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!