ፋሲል ከነማ ለጠለምትና አዲአርቃይ ተፈናቃይ ዜጎች ድጋፍ አደረገ


ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – ፋሲል ከነማ ለጠለምትና አዲአርቃይ ተፈናቃይ ዜጎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

ፋሲል ከነማ ከአዲአርቃይና ጠለምት አካባቢዎች በህልውና ማስከበር ዘመቻው ምክንያት በደባርቅ ከተማ በጊዜያዊነት ለተጠለሉ ከ16 ሺህ በላይ ወገኖች ነው የልብስና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገው፡፡

ድጋፉን ያበረከቱት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚደንት ወጣት ሃይለማርያም ፈረደ፤ ለወገኖቻችን ለጊዜው ይሆን ዘንድ ከ600 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም በጋይንት ግንባር ለተሰለፈው የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ፋኖ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብዮት ብርሃኑ ወገኖቻችን በችግር ላይ ሆነው ቆመን መመልከት የለብንም ብለዋል፡፡

ድጋፉ ከክለቡ ተጫዋቾች፣ የስታፍ አባላት እና ደጋፊዎች መሰብሰቡን ከሰሜን ጎንደር ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት የተኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

በቀጣይም ይህ የህልውና ዘመቻ እንኪጠናቀቅና ወገኖቻችን ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ለማገዝ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡