ፓርቲው በሕዝብ ኅልውና ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት በጋራ መመከት እንደሚገባ ገለጸ

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ኅልውና ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት በጋራ መመከት እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ አሳሰበ።

ፓርቲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በውስጥ ጉዳይዋ ላይ ጣልቃ በሚገቡ የውጭ መንግስታት የተለያየ ጫና እየተደረገባት ይገኛል፡፡ የህወሃት የሽብር ቡድን በንጹሃን ላይ ያደረሰውን ጥፋት ከቁብ ያልቆጠሩት አንዳንድ የውጭ አገራት ዛሬም በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጸመ ሰበብ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ ሲራወጡ ይስተዋላል፡፡

እስካሁን በአገራችን ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም በአገር ውስጥ፣ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም የአገራችንን እውነታ የተገነዘቡ አገራት በጋራ ባደረጉት ሁለንተናዊ ጥረት ብዙዎቹ ሙከራዎች ሊቀለበሱ ችለዋል፡፡

ዛሬም ኢትዮጵያ ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለማሳደር አዲስ ረቂቅ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያውያንን መነሳት የማይፈልጉ የተለያዩ ኃይሎችም ረቂቁን ለማፀደቅ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛል፡፡ ይህ ኤች አር 6600 እና ኤስ 1399 በመባል የሚጠራው ረቂቅ በሰሜኑ ጦርነት ትክክለኛ አጥፊው ማን እንደሆነ በሚዛናዊነት ያላየ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል የደረሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት እውቅና የማይሰጥ ይልቁንም አንድን ወገን ለመደገፍና እና ለመሸፈን የተረቀቀ ለመሆኑ አመላካች ነው፡፡

ይህ ረቂቅ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረውን ጫና በሚገባ በመገንዘብ ኢትዮጵያውያን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአንድ ላይ በመቆም ረቂቁ እንዳይጸድቅ ጫና ማሳደር አለባቸው፡፡ መንግስት የዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመጠቀም የራሱን ኃላፊነት የሚወጣ ሆኖ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ረቂቅ ሰነዱ እንዳይጸድቅ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን መንግስትን ከመደገፍ እና ከመቃወም ጋር ሲያይዙት ይስተዋላል፡፡ ኤች አር 6600 እና ኤስ 1399 መደገፍ ማለት በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ መፍረድ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለረቂቅ ሰነዱ በቂ ግንዛቤ ሳይዙ በግብታዊነት ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን ለመውጋት መጣደፍ ጥፋቱ የጋራ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡