ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ በአንዳንድ የምዕራቡ ዐለም መገናኛ ብዙኃን እንደሚነገረው አይደለም አሉ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ስሟ ተደጋግሞ እንደሚነሳ እና በኢትዮጵያ ያለው እውነታ በአንዳንድ የምዕራቡ ዐለም መገናኛ ብዙኃን እንደሚነገረው አይደለም ሲሉ ገለፁ፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የሁለትዮሽ ጉዳዮች እና ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታን በተመለከተ ከኮትዲቯሩ ፕሬዝዳንት ኦላሳኔ ኦታራ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አክሊሉ ከበደ እንደተናገሩት የኮትዲቯሩ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ መንግስት ህጋዊ መሆኑን እንደሚያምኑ እና በዚህ መንግስት ላይ በህገወጥ መንገድ የሚደረግን እንቅስቃሴ እንደማይቀበሉ እንዲሁም የኢትዮጵያ አቋም ትክክል መሆኑን እንደሚቀበሉ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ላይ ባልተገባ መንገድ የሚደረግ ጫናን እንደማይቀበሉ እና ከፕሬዝዳንቷ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተረዱትን እውነት ለወዳጅ ሀገራት በማስረዳት አብረው ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነትም መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ኮትዲቯር በተባበሩት መንግስታት ሰብኣዊ መብት ምክር ቤት አባላት መካከል አንዷ ስትሆን ሰሞኑን ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ያለውን ሰብኣዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ጉባኤ እንዲጠራ ለቀረበው ሀሳብ ድምፅ አልሰጠችም።