ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ 3 አገራት የነበራቸውን ጉብኝት ማጠናቀቃቸውን አስታወቁ።

ፕሬዝዳንቷ ከአገራቱ መሪዎችና እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ ካሉ ድርጅት ኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ሲመክሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በመጨረሻ ጉብኝታቸው ከጋቦን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ኦዲምባ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተናልም ነው ያሉት፡፡

“የሥራ ጉብኝት ያደረኩበት ሁለተኛ አገር አንጎላ ሲሆን የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ለፕሬዝዳንት ጆአዎ ሉሬንሶ ማብራሪያ ሰጥቻለሁ፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልበት ላይ ሐሳብ ተለዋውጠናል” ብለዋል፡፡

ጉብኝት በጀመሩባት ኮት ዲቯርም በተመሳሳይ ከፕሬዝዳንት ኦላሳን ኦትራ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የአገራቱ ግንኙነት ስለሚጠናከርበት ስልት መምከራቸውን ነው ፕሬዝዳንቷ የጉብኝታቸውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በቲውተር ገጻቸው የጻፉት፡፡