ሀገሪቷ ከወጣቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም አላገኘችም – አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ

አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ

ኢትዮጵያ  ካላት አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር 70 በመቶ የሚሆነው ከ30 ዓመት በታች የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም ሀገሪቷ ከወጣቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም አላገኘችም ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ እንደምክንያት የሚነሳው ወጣቱ ላይ ሊሰራ የሚገባው ስራ በአንድም በሌላ ምክንያት ባለመሰራቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የወጣቶችን ሀገራዊ ሚና ማሳደግ እና  በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ መፍጠር ለሀገር ግንባታ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ወጣቶችን ያላሳተፈ ማንኛውም እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆን እንደማይችል ገልጸዋል ፡፡

በኢትዮጵያ የነበሩ ስርዓቶች ወጣቱ ለሚፈልገው ሳይሆን ስርዓቱ ለፈለገው አላማ ብቻ መጠቀሚያ ሆኖ ቆይቷል ያሉት ዳይሬክተሩ እንደሀገር ለሚስተዋለው ችግር ዋነኛ መንስኤ በመሆኑ ወጣቱ ለችግር ተጋላጭ እንዳይሆን  ቤተሰብ ፣ ትምህርት ቤቶች፣  የሀይማኖት ተቋማት እና  መንግስት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ተሳታፊ እንዲሆኑና የሀገር ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ የስብዕና ግንባታ ሥራ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም አቶ ዳግማዊ ተናግረዋል፡፡

(በህይወት አክሊሉ)