ሀገራዊ ሁኔታውን ግምት ውሰጥ ያስገባ ፈጣን ምላሽ መስጠት የቅድሚያ ተግባር ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አቶ ደስታ ሌዳሞ

ጥቅምት 23/2014 (ዋልታ) ወራሪው የትሕነግ ኃይል ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት የከፈተብንን ጦርነት በድል ለመቋጨት አሁን ያለውን ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ግምት ውሰጥ ያስገባ ምላሽ መስጠት የቅድሚያ ተግባር መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለፁ።

የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ  ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በተላለፉ ውሳኔዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሁሉም የሚሆነው ሀገር ስትኖር ነው፤ የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ ደግሞ የሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ የጋራ የሃላፊነት ነው ያሉት ርዕሰ መሰተዳድሩ መላው የክልሉ ህዝብ ዛሬ ነገ ሳይል ሁለንተናዊ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ወደ ግንባር መዝመት፤ አካባቢን ከሰርጎ ገቦች መጠበቅ እና ለሠራዊቱ የሚደረጉ የሞራል እና የአይነት ድጋፎችን ማጠናከር የገጠመንን የህልውና አደጋ በድል ለመወጣት ዋናው  ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ እና ፈጣን የሆነ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ይጠበቃልም ብለዋል።

ከወራሪው ሃይል ጋር በመቀናጀት መረጃ በማቀበል፤ ለሠርጎ ገቦች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በየአከባቢው የሚሰሩ የቡድኑ ተባባሪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

መከላከያ ሰራዊት እና ጥምር ጦሩ በየተሠማራበት አውደ ውጊያ ሁሉ ዋጋ እየከፈለ    የሀገሩን ሉዓላዊነት እያሰጠበቀ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ነገር ግን በተቃራኒው  የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ህዝብን የሚያሸብሩ እና የስነ-ልቦና የበላይነትን ለመያዝ በየአካባቢው እየሰሩ ያሉ ግለሰቦች ከድርጊታው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።

እንደ ኢብኮ ዘገባ የክልሉ መንግስትም ሁኔታዎችን በጥንቃቄ እየተከታለ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት በማናቸውም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ህግ ለማስከበር በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።