ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) አሸባሪውን የሕወሓት ወራሪ ኃይል ለመቀልበስ የፈጠርነውን ሀገራዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላምና ለሃገር ግንባታ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ “ከጦርነት ወደ ብልፅግና በሰላም ጎዳና” በሚል በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመዲናዋ አመራሮች፣ ከክፍለ ከተሞች ተቋማት፣ ከመንግስትና ከግል ሚዲያ አመራሮችና ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም መምህራን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከንቲባዋ አሁን ላይ በአሸባሪው ቡድን የተቃጣብንን ወረራ ለመቀልበስ በሁሉም መስክ የፈጠርነውን ሀገራዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሰላምና ለሃገር ግንባታ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና በሃገር ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና መረጋገጥ ላይ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል፣ የሚዲያና የኪነ- ጥበብ ባለሙያው ሙያዊ ኃላፊነት ትልቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ለመፍታት እንዲሁም በወራሪው ቡድን የወደሙ አካባቢዎችንና መሰረተ ልማቶችን መልሶ በማቋቋምና በወራሪው ቡድን የተያዙ ቀሪ አካባቢዎችን ነፃ በማድረግ ረገድ የሚጠበቁ ሚናዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
የተጎዳውን ኢኮኖሚ በመገንባትና የብልፅግና ግባችንን በማሳካት በኩል የታየዉን ከፍተኛ ኅብረ ብሔራዊ መነሳሳትና አንድነት አሟጦ መጠቀም ከሁላችንም ይጠበቃል ያሉት ከንቲባዋ መሰል ውይይቶች በመላው ከተማ በሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል እንደሚካሄድ በማኅበራዊ ተስስር ገፃቸው አስታውቀዋል፡፡