ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሃገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ መርሃ ግብር ይፋ አደረገ፡፡
ሁለተኛው ዙር በአይነቱና በይዘቱ ለየት ያለ ሀገር አቀፍ የጸሎትና ምህላ ሳምንት መታወጁን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ፣ የሰላምና መረጋጋት እጦት እንዲሁም ብሄርና ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገ ግድያ መበራከት ሀገራዊ የጸሎትና ምህላ ሳምንት እንዲታወጅ አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በጎረቤት ሀገራት ምስራቅ ቀጠና ላይ የሚታየው የድንበር አለመግባባቶችን በሚመለከት የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሀገራዊ ጸሎት ማድረግ ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በዚህ አሳሳቢ ወቅት ስለሆነውና እየሆነ ስላለው ሁሉ በደልና ጥፋት በፈጣሪ ፊት በመቅረብ በንስሃ ከራስና ከፈጣሪ ጋር እርቅ መፈጸም እንደሚገባ ያሳሰቡት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፣ የጋራ መርሃ ግብሩ ሚያዝያ 7 ከቀኑ 9 ሰዓት እንደሚታወጅ አስታውቀዋል፡፡
መርሃ ግብሩም የሁሉም እምነት ተቋማት፣ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች በይፋ እንደሚታወጅ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ከሚያዚያ 8 ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚቆይ በሁሉም አባል የሃይማኖት ተቋማት በተናጠል የሚዘጋጅ ጸሎትና ትምህርት በመገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች ይተላለፋልም ተብሏል፡፡
በመገናኛ ብዙሃን በሚተላለፍ ፕሮግራም የ1 ሳምንት ቆይታ በሚኖረው የቴሌቪዥን ስርጭት ከምሽት 3 እስከ 4 ሰዓት እንዲተላለፍ የሚደረግ ነው፡፡
ካለፈው ዓመት በተለየ መልኩ ዜጎች ከፈጣሪ ጋር በመቀራረብ በሀገሪቱም ላይ ፍትህ እንዲሰፍን ምርጫውም ሰላማዊ እንዲሆን በምልጃ የሚቀረብበት መሆኑንም ጠቅላይ ፀሐፊው አመልክተዋል፡
ወቅቱ በኦርቶዶክስ አብይ ጾም እና በሙስሊም እምነት ተከታዮች ዘንድ ደግሞ የረመዳን ጾም የሚከናወንበት እንዲሁም ሌሎች እምነት ተቋማት ለመልካም ተግባራት ተባባሪ በመሆናቸው የተወሰነ ስለመሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ጸሎትና ምህላ የሃይማኖት ተቋማት ችግር መፍቻ እንደሆነ ታምኗል፤ የታመነበት በዚሀም ኢትዮጵያውያን በታሪክ በጋራ ተሻግረው የመጡ በመሆናቸውም ዛሬም የተደቀነባቸውን ፈተናዎች በጋራ እንደሚያልፉ የሚጠበቅ ስለመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በተቀሩት ቀናት ስለ ይቅርታ፣ ርህራሄ፣ ተስፋ፣ እምነት፣ ፍቅር እና ምስጋና በተመረጡ ርዕሶች ተከታታይ ትምህርቶችን ተደራሽ በማድረግ እንደመክፈቻው ሁሉ አርብ ሚያዚያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በልዩ ዝግጅት የመዝጊያ መርሃ ግብር እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገልጿል፡፡
(በሰለሞን በየነ)