ሁለተኛው ሀገራዊ የትርጉም ጉባኤ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የትርጉም ጉባኤ “Translation for National Consensus” በሚል በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ነው።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች ባህሎችና እምነቶች ያሉባት ሀገር ናት ያሉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ቋንቋዎቹ የያዙትን እምቅ እውቀትና እሴት ለሌላው ማህበረሰብ ለማሳወቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ 53 በሚሆኑ ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠባቸው መሆኑም ተነግሯል።

ጉባኤው በትርጉምና በአስተርጓሚነት ሙያ ዙሪያ ጠንካራ ውይይት በማድረግ ሙያው ለሀገራዊ አንድነትና መግባባት የሚያደረገውን አስተዎፅኦ ለይቶ በማውጣት ለመንግስት የፖሊሲ ግብዓት የሚሆን ሀሳብ ለማሰባሰብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

የሀገራችንን ቋንቋዎች ሰዎች በቀላሉ መረዳትና ማወቅ እንዲችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል የተባለ ሲሆን አንደኛው ማህበረሰብ የሌላውን ማህበረሰብን ቋንቋ ለመማር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ለብሔራዊ መግባባት  ምቹ መደላደል ይፈጥራል ተብሏል።

ሚኒስቴሩ ከስምንት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር የትርጉምና የአስተርጓሚነት ሙያ ለማዳበር እንዲሁም የሰው ሀይል ለማፍራት የሚያስችል መነሻ ስርዓተ ትምህርት ማዘጋጀቱ ነው የተነገረው።

በጉባኤው የፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የከፍተኛ ትምህርት ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ሲሆን ትርጉምና የትርጉም ስራን በተመለከተ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ይደርግባቸዋል ተብሏል።

ምንይሉ ደስይበለው (ከአዳማ)