ነሃሴ 4/2013(ዋልታ) – ሁለተኛው ምዕራፍ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የተጠቃሚዎች ምዝገባ መጀመሩን የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ ፡፡
የምግብ ዋስትና ልማታዊ ሴፍትኔት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስ እንደገለፁት የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ ዋስትናቸዉን ለማረጋገጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በ11 ከተሞች ተተግብሯል ብለዋል ፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለፁት እስካሁን በአካባቢ ልማት የተሰማሩ ተጠቃሚዎች ደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ፣ በውበትና አረንጓዴ ልማት ፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ፣ በከተማ ግብርና እንዲሁም በመሰረተ ልማት ዘርፍ በመሰማራት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል ፡፡
አያይዘውም በመጀመሪያ ዙር ወደ ፕሮግራሙ ገብተው ሶስት ዓመት የሞላቸውን ተጠቃሚዎች በኤጀንሲው የተለያዩ የድጋፍ ማዕቀፎች ተደርጎላቸው በማህበረሰብ አቀፍ የልማት ስራ የተሳተፉ ተጠቃሚ ማህበረሰቦች በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ማሸጋገር ተችሏል ብለዋል ፡፡
በተጨማሪም በተያዘው በጀት ዓመት ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ መቶ ዘጠኝ ሺህ ዘጠኝ መቶ አስራ ስምንት ዜጎችን በሁለተኛው ምዕራፍ ከሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በ 11 ክ/ከተሞች በ124 ወረዳዎች በ827 ክላስተሮች የቤት ለቤት ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል ሲሉ አቶ ታምራት እስጢፋኖስ ገልጸዋል፡፡
(በአመለወርቅ መኳንንት)