ሁለተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ምርምር ኮንፈረንስ መካሄድ ጀመረ


ሰኔ 17/2014 (ዋልታ)
ሁለተኛው ዓመታዊ የፓርላማ የምርምር ኮንፈረንስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ መካሄድ ጀመረ።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ኮንፈረንሱን ሲያጀምሩ የሀገርን ማኅበራዊ፣ ምጣኔ-ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን ለማሳደግ ጊዜውን የዋጁ ጥናትና ምርም ሥራዎች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
አፈ ጉባኤው ምክር-ቤቱ የሚያከናውናቸውን መደበኛ ሥራዎች በምርምር እና በጥናት በማስደገፍ ችግር ፈቺ ሕጎችን ለማውጣት ፣ የአሠራር ለውጥ የሚፈልጉ አሳሪ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ለማስተካከል ጥናት እና ምርምር ያስፈልጋል ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፓርላማው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ለመቆጣጠር፣ ለመከታተል እና ለመደገፍ በምርምር እና በጥናት በተደገፉ ሥራዎች መታገዝ አለበት ብለዋል።
በዚህም ረገድ የትምህርት ሚኒስቴር ፓርላማውን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ዋና ፀሃፊ ሄኖክ ስዩም (ዶ/ር) ደግሞ፤ በዚህ ኮንፈረንስ በምርምር ሥራዎች የሚገኙ አዳዲስ የምርምር ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን ለምክር ቤቱ በመቀመር፣ ለሚያወጣቸው ሕጎች በግብዓትነት እንደሚጠቀም አመልክተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ፤ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች፣ የሲቪክ እና የሙያ ማኅበራት ተወካዮች እና የምክር ቤቱ አመራሮች እና አባላት እየተሳተፉ እንደሚገኝ ከምር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።