ሁለቱ ሚኒስቴሮች የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ ሁለቱ ተቋማት የተናበበና የተቀናጀ አሰራር እንዲሁም የጠራ የመረጃ ሥርዓትን ለመዘርጋት ያስችላቸዋል ነው የተባለው፡፡
በዚህም የሃብትና የጊዜ ብክነትን በመቅረፍ አገር ወዳድ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር የሥራ ስምሪት በሚፈለገው መጠን በማቅረብ ለአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ ምርትና አገልግሎትን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የበቃ የሰው ኃይል መገንባት፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የኢንተርፕርነርሺፕና የሥራ ፈጠራ ልማት፣ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት አገልግሎትን ማጠናከርና ማስፋፋት የስምምነቱ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚልና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ታድመዋል፡፡
በሳሙዔል ሓጎስ