ሁሉም የስኳር ፋብሪካዎች እስከ ኅዳር አጋማሽ ጥገናቸውን አጠናቀው ወደ ምርት ይገባሉ ተባለ

ጥቅምት 8/2015 (ዋልታ) ሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች እስከ ኅዳር አጋማሽ ድረስ የክረምት ጥገናቸውን አጠናቀው ወደ ምርት የሚገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ አስታወቀ።

2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ ለማስገባት የባንክ ሂደቱ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ሂደቱ እንደተጠናቀቀም በ45 ቀናት ውስጥ ስኳሩ ወደ አገር የሚገባ መሆኑን በኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ዋና ክፍል ኃላፊ ረታ ደመቀ ገልጸዋል።

ከውጭ መግባት ያለበት የስኳር ምርት በዓለም እና አገር አቀፍ ወቅታዊ ሁኔታዎች ሳቢያ ባጋጠመ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የዋጋ መናር ሳቢያ መጓተቱ አሁን ላይ ለሚታየው የስኳር እጥረት ድምር ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

የስኳር ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ በተለያዩ የግንባታ ደረጃ የሚገኙ የስኳር ፋብሪካዎች እና ፕሮጀክቶች ግሩፑ እንዲያስተዳድር እና ራሳቸውን ወደሚችሉበት ደረጃ የማሸጋገር ሥራ እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶት የተለያዩ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል።

ለስኳር እጥረት መከሰት ምክንያቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው የፋብሪካ፣ የመስኖ አውታር ማሽነሪዎች፣ ልዩ ልዩ ተሸከርካሪዎችና መለዋወጫዎች፣ ልዩ ልዩ ኬሚካሎች፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የጸረ-አረም መድሃኒቶችንና ግብዓቶችን ከውጭ ገዝቶ ለሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች ለማቅረብ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የዋጋ ግሽበት ማጋጠሙ ናቸው ብለዋል።

በአገሪቱ እየታየ ያለው የጸጥታ ችግር የስኳር ፋብሪካዎችን የምርት ሂደት በተደጋጋሚ ያስተጓጎለበት እና ልዩ ልዩ ግብዓቶች እንዳይቀርቡላቸው እንዳደረገ መጠቆሙን የኢብኮ ዘገባ አመላክቷል።

የአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የስኳር ፍጆታ ከ5 እስከ 6 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል ያሉት ኃላፊው፣ ኢትዮጵያ በአመት ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር የምታመርት ሲሆን ቀሪውን ኮታ ለማሟላት በየዓመቱ ከ1 እስከ 2 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ ታስገባለች ብለዋል።

ስምንት የስኳር ፋብሪካዎችን ለግል ኩባንያዎች በከፊል እና በሙሉ እንዲተላለፉ ዓለም አቀፍ ጨረታ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ወጥቶ በሂደት ላይ እንደሚገኝ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል።