”ሃና ፋውንዴሽን” ለተፈናቃዮች 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 19/2014 (ዋልታ) መቀመጫውን በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ያደረገው ”ሃና ፋውንዴሽን” የተሰኘ ድርጅት በሰሜን ወሎ ዞን ሃብሩ ወረዳ ድሬ ሮቃ ጃራ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰባት ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአልባሳት ድጋፍ አደረገ።

በዞኑ ከ73 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠሊያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተገልጿል።

የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር የ”ሃና ፋውንዴሽን”ን የአልባሳት ድጋፍ በአዲስ አበባ ትረስት ፈንድ በኩል ዛሬ ተረክቧል።

የትረስት ፈንዱ ተወካይ ዮናስ ሸዋዬ የአልባሳት ድጋፉ በሁሉም እድሜ ክልል የሚገኙ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል በበኩላቸው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ተፈናቃዮች በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከቀዬያቸው ለቀው የሸሹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ከ73 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙና መንግስት፣ ረጂ ድርጅቶች፣ ግለሰቦችና ባለሃብቶች ለዜጎቹ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ መገለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዲያስፖራውና ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተፈናቃዮች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዋና አስተዳደሪው ጥሪ አቅርበዋል።