ህወሃት በጦርነት ያስጨረሳቸውን ህጻናት አስከሬን በመንግስት በጅምላ የተፈፀመ ግድያ ለማስመሰል እየሞከረ ነው

ሐምሌ 25/2013 (ዋልታ) –  አሸባሪው ህወሃት በሀሺሽ አስክሮ በጦርነት ያሰጨረሳቸውን ህጻናት አስከሬን በመንግስት በጅምላ የተፈፀመ ግድያ ለማስመሰል እየጣረ መሆኑን ምንጮች አስታውቁ።

ምንጮቻችን እንደገለፁት አሸባሪው ህወሃት በአውደ ውጊያው ያጣውን ድል በቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ለማግኘት እየተፍጨረጨረ ነው።

በተለይ ሰሞኑን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓዎር ወደ “ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው” የሚለው ዜና ከተሰማ በኋላ የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳውን በመንዛት መንግስትን ለመክሰስ እየሞከረ መሆኑ ን ምንጮች  ለኢዜአ አረጋግጠዋል።

የሽብር ቡድኑ የህጻናትን አስከሬን በመንግስት የተገደሉ አስመስሎ ለማቅረብ ሽር ጉድ እያለ እንደሚገኝ ከስፍራው ያሉ ምንጮቻችን ጠቁመውል።

የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ከወጣ በኋላ አሸባሪው ህወሃት በክልሉ በእምነታቸው፣ በፖለቲካ አቅማቸው ሰዎችን እየገደለ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ ቡድኑ  የትግራይ ተወላጆችን “የጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ናችሁ” እንዲሁም “የመከላከያ ሠራዊቱን ቀልባችኋል” እና ሌሎች ምክንያቶችን በመደርደር የክልሉን ተወላጆች እየገደለ መሆኑን ጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረገው ቆይታ አጋልጧል።

ቡድኑ እስከቅርብ ቀናት ድረስ ከ450 በላይ ንጹሃንን የገደለ ሲሆን፤ በውቅሮ፣ በአክሱምና በሌሎች አካባቢዎች በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ያተኮረ ጥቃት መሰንዘሩንም ነው ጋዜጠኛው ያሳወቀው።

በሌላ በኩል የሽብር ቡድኑ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህጻናትን በማስገደድና ከሶስት ቀናት ያልበለጠ ስልጠና በመስጠት ለጦርነት ሲያሰማራ መቆየቱን ያስታወሱት ምንጮቻችን፤ በአሁኑ ወቅት የደረሰበትን ከባድ ሽንፈትና ኪሳራ ለመሸፈን ፍጹም ከሰብዓዊነት በወጣ መልኩ የህጻናቱን አስከሬን መንግስት እንደጨፈጨፋቸው ለማስመሰል መቀሌ ላይ ማከማቸቱን ጠቅሰዋል።

የህጻናቱን አስከሬን በማሰባሰብ “የኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊት ገደላቸው” ብሎ በውጊያ ያስጨረሳቸውን ህጻናት መነገጃ ለማድረግ የተለመደውን የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ለማሰራጨት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ምንጮቹ አረጋግጠማል።

መንግስት የትግራይ ህዝብ የመኸር እርሻ ተረጋግቶ እንዲያከናውንና በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ የተናጥል ተኩስ አቁም ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም አሸባሪው የህወሃት ቡድን ህጻናትን በሀሺሽ በማስከር ወደ ጦርነት በማሰማራት በትግራይ አጎራባች ክልሎች ላይ ጥቃትና ዘረፋ እየፈጸመ ይገኛል።

አሸባሪ ቡድኑ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመመከት ኢትዮጵያውያን እየሰሩ ሲሆን፤ ከዚህ አኳያ የሽብር ቡድኑ ህጻናትንና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ሳይቀር ወደ ጦርነት በማሰማራት አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸመ እንደሚገኝ መዘገቡ ይታወሳል።

የሽብር ቡድኑ ይህ አልበቃ ብሎት በሀሺሽ እያሰከረ በጦርነት በአሰማራቸው ህጻናት ህይወት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተውተረተረ መሆኑም ነው የተገለጸው።

በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሃት በህጻናት ህይወት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየጣረና የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸ ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታን መምረጡ ብዙዎችን አሰገርሟል።

የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ከወጣ በኋላ አሽባሪው ህወሃት በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ግፍ ከዕለት ተዕለት እጅግ እየከፋ መምጣቱን መዘገቡ ይታወሳል።