ነሀሴ 07 ቀን 2013 (ዋልታ) – ህወሃትና ሽኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በጋራ ሲሰሩ የቆዩ የሽብር ቡድኖች ናቸው፤ ጋብቻቸውም አዲስ ጉዳይ አይደለም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጅታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ወቅታዊ አገራዊ ጉዳይን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጭ ሀገራት ሚዲያ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ኃላፊዋ በመግለጫቸው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ ሸኔን በመጠቀም የሽብር ስራውን ሲያከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል።
መንግስት ሁለቱ ቡድኖች ሀገር ለማፍረስ በጋራ እየሰሩ መሆኑን በተጨባጭ መረጃ በመገንዘብ በአሸባሪነት ፈርጇቸዋል ብለዋል።
ከዚህ አንጻር በቅርቡ ሁለቱ የሽብር ቡድኖች “ጋብቻ” መፈጸማቸውን ማወጃቸው አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ የሽብር ቡድኖቹ ሀገር ለማፍረስ በጋራ እንደሚሰሩ በግልጽ ያረጋገጡበት ሆኗል ብለዋል።
መንግስት የሁለቱን ሽብር ቡድኖች በሚመለከት ያለውን ምልከታ ትክክለኝነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያረጋገጠ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኖቹ ቆምኩለት የሚሉትን ህዝብ በመግደልና በማሰቃየት እንደሚታወቁ አስታውሰው፤ የፈጠሩት ጋብቻም የትግራይና ኦሮሞ ህዝቦችን እንደማይወክል አረጋግጠዋል።
በተጨማሪ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ሲመራ በቆየባቸው ጊዜያት የኦሮሞ ወጣቶች “ኦነግ ናችሁ” በሚል ሰበብ አሰቃቂ ግድያ፣ ድብደባና ግፍ ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም የሁለቱን የሽብር ቡድኖች “ጋብቻ” ለዘመናት ለኦሮሞ ህዝብ መብት ሲታገሉ በቆዩት አንጋፋ የፖለቲካ ልሂቆች ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።