ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ደም ለማቃባት ትንኮሳ ማድረጉ ተቀባይነት የለውም

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ደም ለማቃባት ትንኮሳ ማድረጉ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ሲሉ አቶ ሃይለ ረዳ ገለጹ።

አቶ ሃይለ ረዳ የአሸባሪው ህወሃት ቃል አቀባይ የጌታቸው ረዳ ወንድም ናቸው።

በአፋር ክልል ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋ መምህሩ ሃይለ ረዳ፤ አሸባሪው ህወሃት “ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ” በማለት እንቅስቃሴ መጀመሩ የአገር ክህደት መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ የአገር ዳር ድንበር የሚጠብቀውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን ድንገት በማጥቃት የፈፀመው ዘግናኝ ድርጊትም በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያ አላስፈላጊ ግጭትና ጦርነት እንዲካሄድ አሸባሪው ህወሃት ቆርጦ በመነሳት የችግሮች ሁሉ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የትግራይን ህጻናት ለጦርነት መልምሎ በማሰለፉ ከፍተኛ ወንጀል እየፈፀመ ይገኛል ነው ያሉት መምህር ሃይለ ረዳ።

የግለሰቦችን ስልጣን ለማስጠበቅ ሲባል ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ ህይወታቸው እንዲቀጠፍ በማድርግ የትግራይ ክልል ነዋሪ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዲገባ እያደረጉት መሆኑን አመልክቷል።

በአፋር ጋሊኮማ ንጹሃን ዜጎችን በመጨፍጨፍ የሽብር ቡድኑ የፈፀመውን የጭካኔ ተግባርም አውግዘዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።