ህወሓትን ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውን የሰለጠኑ ተጠባባቂ ኃይሎች ገለጹ

ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ ለመመከትና አሸባሪው የህወሓት ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም ዘርፍ ዝግጁ መሆናቸውን ወታደራዊ ስልጠና ወስደው የተመረቁ የደሴ ከተማና ዙሪዋ ተጠባባቂ ኃይሎች ገልጸዋል፡፡

አሸባሪውን ቡድን በአጭር ጊዜ ለመደምሰስ የሚያስችል ቁመና ላይ መሆናቸውንም ነው ወጣቶቹ የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ለማስቀጠልና ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግ በሚደረገው በዚህ ዘመቻ ላይ መሳተፋቸው እንዳስደስታቸውም ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና በማስጠበቅ የጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ ለመድገም ዝግጁ ነን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

የደሴ ከተማ ከንቲባ አበበ ገብረመስቀል የተጠባባቂ ኃይል አባላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ለማረጋገጥና ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ለሚደረገው የህልውና ዘመቻ ተሳታፊ በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

በዘመቻው የኢትዮጵያ አሸናፊነት የተረጋገጠ ሐቅ መሆኑንም ከንቲባ አበበ ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ አባት አርበኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና የደሴ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡