ህወሓት እስኪወገድድረስ ለሰራዊቱ የምናደርገውን ድጋፍ እንቀጥላለን – የቤንች ሸኮ ዞን ሴቶች

ሐምሌ 22/2013 (ዋልታ) – ሀገር በማፍረስ ተግባር የተሰማረው ህወሓት ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ለሠራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጠሉ በቤንች ሸኮ ዞን የሚገኙ ሴቶች አስታወቁ።

“ስንቅ ለጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ዛሬ ስንቅ የማዘጋጀት ሥራ ተጀምሯል።

በዞን ማዕከል የስንቅ ዝግጅት ሥራ የተሳተፉት የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ብርቅነሽ ባድኒስ እንዳሉት የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ ጦርነት ከፍቶ ወረራ እያካሄደ ነው።

የጥፋት ቡድኑን ለመደምሰስ ለተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አለኝታነታቸውን ለማሳየት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሀገር ጉዳይ ሴት ወንድ ሳይባል በጋራ መነሳት እንዳለበት ጠቁመው “በተለይ ሴቶች ሠራዊቱን በስንቅና በሞራል የመደገፍና የማበረታታት ሚናችንን ልናጠናክር ይገባል” ብለዋል።

“መከላከያ ሠራዊታችንን ባለን አቅም ሁሉ በመደገፍ አጋርነታችንን እናጠናክራለን” ያሉት ደግሞ የዞኑ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች መልካሙ ናቸው።

በተለይ ለሠራዊቱ ወገንተኝነታቸውንና አጋርነታቸውን በማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለድል እንዲበቃ በሁሉም መስክ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

ሌላው የስንቅ ዝግጅቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ሽታዬ ድንቃ በበኩላቸው በስንቅ ዝግጅት ሳይወሰኑ በግንባር ጭምር ዘምተው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክትዋል።

“እኛ እያለን የመከላከያ ሠራዊቱ መራብና መጠማት የለበትም” ያሉት ወይዘሮዋ በቀጣይም ካላቸው ላይ በማካፈል በስንቅ ዝግጅቱ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የዞኑ ሴቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ባዋጡት ግማሽ ሚሊዮን ብር የስንቅ ዝግጅት ሥራው ዛሬ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ዳዲ ናቸው።

ኃላፊዋ እንዳሉት በስንቅ ዝግጅቱ ማር፣ በሶ፣ ዳቦ ቆሎና ሌሎችም ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ ሚቆዩ ደረቅ የምግብ ዓይነቶች ይዘጋጃሉ።

በሥራውም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ሴቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የዞኑ ሴቶች ሀገር በማፍረስ ተግባር የተሰማራው የህወሓት የጥፋት ቡድን ሙሉ በሙሉ እስከሚደመሰስ ድረስ የጀመሩትን እገዛ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ሴቶቹ በስንቅ ዝግጅት ሥራው ብቻ ሳይወሰኑ ለሠራዊቱ ደም በመለገስ ጭምር የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል