ህወሓት በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች መረጃ ቋት ውስጥ የተካተተ መሆኑን መረጃዎች ጠቆሙ

ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ህወሓት በሽብር ተግባሩ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች መረጃ ቋት ውስጥ የተካተተ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

አሜሪካዊው ጋሪ ላ ፍሪ በአሜሪካው የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የፓርክ ኮሌጅ ዳይሬክተር፣ የወንጀል ምርምር እና የኢኖቬሽን ዳይሬክተር እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሽብር ላይ ጥናት የሚያደርግ ተቋም መስራች  የሆኑ ስመ ጥር ባለሙያ ናቸው።

በዋናነት በእኝህ ስመጥር ፕሮፌሰር እና በአሜሪካ ብሔራዊ የሽብር እና የሽብር ግብረ መልስ ጥናት ማዕከል አማካኝነት እአአ በ1970 የተመሠረተ ዓለም አቀፍ የሽብር እና ሽብርተኞች መረጃ መመዝገቢያ ቋት (GlOBAL TERRORISM DATABASE) የሚባል የመረጃ ማዕከል አለ።

ይህ የመረጃ ቋት እንደ አልቃይዳ ያሉ አሸባሪ ድርጅቶች የፈጸሟቸውን ከ200 ሺህ በላይ የሽብር ወንጅሎችን ከእነ ፈጻሚዎቻቸው መዝግቦ ይዟል።

አሸባሪው ህወሓትም የፈጸማቸው የሽብር ወንጀሎችና ራሱ ድርጅቱ በዚህ ዓለም አቀፍ የሽብር መረጃ ቋት ውስጥ ከ45 አመት በፊት ጀምሮ አሸባሪ ተብሎ ተመዝግቦ ይገኛል።

ይህ አሸባሪ ድርጅት የሽብር ተግባር መፈጸም ብዙዎች እንደሚያስቡት የአሁን ተግባሩ ሳይሆን ገና ከጅምሩ ሲፈጠር አንስቶ የተካነበት መሆኑን ይሄው ዓለም አቀፍ የመረጃ ቋት ውስጥ ተመዝግቦ ያለው መረጃ ያሳያል።

አሸባሪው ህወሓት ከስር የተያያዘው የመረጃ ቋቱ እንደሚያሳየው እአአ ከ1976 ጀምሮ በተለያዩ ንጹሀን ዜጎችና ንብረቶች ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃት ፈጽሟል።

ይህ አሸባሪ ድርጅት የፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች በሙሉ ኢላማ ያደረጉት ንጹሀን ዜጎችን፣ የሀይማኖት ተቋማትን፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ሚዲያዎችን እና መሰል የግለሰብ ንብረቶች ላይ ነው።

አሁንም ይህ አሸባሪ ድርጅት ተመሳሳይ ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል፡፡