ህወሓት በጋሊኮማ የፈፀመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ የ3 ቀን ሀዘን ታወጀ

ነሃሴ 5/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ በጋሊኮማ ጊዚያዊ መጠለያ  በነበሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሀዘን ቀን እንዲሆን የአፋር ክልል መንግስት አውጇል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሚና ሴኮ በሰጡት መግለጫ አሸባሪው ህወሓት በጋሊኮማ በንፁሀን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ እጅግ ዘግናኝ እንደነበር ገልፀው የክልሉ መንግስትም ይህን ጥልቅ ሀዘን አስመልክቶ የሶስት ቀናት ሀዘን ማወጁን ገልፀዋል።

ይህንንም ዘግናኝ ጭፍጨፋ አስመልክቶ በአፋር ክልል ውስጥ ከዛሬ ነሀሴ 05 /2013 እስከ ነሀሴ 07/2013 ድረስ የሀዘን ቀን እንዲሆንና የአፋር ክልል ባንዲራም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ የክልሉ መንግስት መወሰኑን ከአፋር ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ታሪክ የማይረሳው 107 ህፃናትን፣ 89 ሴቶችን እና 44 አዛውንቶችን ህይወት የቀጠፈው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ያካሄደው አሸባሪው ህወሓት ድንገት በከፈተው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ንፁሃን አርብቶ አደሮች መገደላቸውና መቁሰላቸው እንዲሁም በመጋዝን የነበረ የአስቸኳይ እርዳታ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ይታወሳል።

አሸባሪው ህወሓት ገና ቀድሞ በረሀ እያለ የነበረውን የአፋርን መሬት ወደ ራሱ የማካለል ቅዠት በግርግር መፈፀም የሚያስችለው መስሎት በፈፀመው ወረራ አርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የጥቃት ሰለባ አድርጎታል ተብሏል።