ህወሓት ትንኮሳ ያደረገባቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎች ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን አስለቀቀ

ነሐሴ 11/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው የህወሓት ቡድን ትንኮሳ ያደረገባቸውን ስትራቴጂክ ቦታዎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን አስለቀቀ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ቆቦ ከተማን በመቆጣጠር ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በቀላሉ ለማለፍ በተለምዶ የአርሴማ ተራሮች የተባሉ አራት ተራሮችን እስከ ሀምሌ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተቆጣጥሮ ለቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ነበር።

ሆኖም የፌዴራል ፖሊስ ሰሜን ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን አራት ፈጥኖ ደራሽ አባላት ከመከላከያ ሠራዊና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት አነስተኛ የሰው ሃይልና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ብቻ በመጠቀም በርካታ የጁንታውን ሃይል በመደምሰስ አራቱንም ተራሮች በአንድ ቀን በማስለቀቅ ለአካባቢው ሚሊሺያ ማስረከብ መቻላቸው ተገልጿል፡፡

አባላቱ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌላ ግዳጅ ለመሰማራት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ትእዛዝ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም የሰሜን ዳይሬክቶሬት ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ሻለቃ ምክትል አዛዡ ኢ/ር ሀሰን አብዱ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ህዝቡን ከጎናችን በማሰለፍና አሸባሪውን እስከመጨረሻው ለማጥፋት መስዋትነትም ጭምር ለመክፈል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል ማለታቸውን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።