ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመደገፍ ሊሆን ይገባል – ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል

ሚያዝያ 14/2014 (ዋልታ) ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከበር የተቸገሩትን በመርዳትና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል አሳሰቡ።

የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የምዕራብ ወለጋ፣ የቄለም ወለጋና የደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የትንሳኤን በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ክርስቲያኑ አብሮነቱንና አንድነቱን በማጠናከር እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት በዓለ ትንሳኤውን ሊያከበር ይገባል ብለዋል።

በዓለ ትንሳኤ ክርስቶስ የአዳም ዘርን ነፃ ያወጣበት ክብረ በዓል በመሆኑ ምዕመኑ የዘረኝነትና የጎሰኝነት አስተሳሰቦችን በማስወገድ በዓለ ትንሳኤውን በአንድነትና በመደጋገፍ እንዲያሳልፈው አሳስበዋል።

በጋምቤላና በቤሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ ህዝበ ክርስቲያን በዓሉን በፍቅርና እርስ በእርስ በመረዳዳት እንዲያከብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቱ ለተጀመረው የሰላም ግንባታና የለውጥ ጉዞ ስኬታማነት ምዕመኑ የበኩሉን እንዲያበረክት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ጥሪ አቅርበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።