ህዝቡ መከላከያን ለመቀላቀል እያሳየው ያለው ተነሳሽነት

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

መስከረም 03/2014 (ዋልታ) ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ እና የህዝቡ መከላከያን ለመቀላቀል እያሳየው ያለው ተነሳሽነት ለጥፋት ኃይሎች የሞራል ሥብራት ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስቴር ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ተናገሩ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት የኢትዮጵያ ህዝብ እያደረገው ያለው ርብርብ ለመከላከያ ሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጭ ላለው ዲያስፖራ ሁሉ ወኔ ሆኗል ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፣ ከአርሶ አደር እስከ አርብቶ አደር፤ ከተማሪ እስከ አስተማሪ በየትኛውም ዘርፍ የተሰማራ ሁሉ ለመከላከያ ያለውን ድጋፍ አሳይቷል፤ ይህ በሀገሪቱ ታሪክ በደማቁ የሚጻፍ ነው ብለዋል።

ህዝቡ በነቂስ ለመከላከያ ድጋፍ መውጣቱ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ እንደሚሆንና ለማሸነፍም የስነ ልቦና ሙሉነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ለሀገሩ ወታደር መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢፕድ እንደዘገበው ህብረተሰቡ የገንዘብና ስንቅ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ግንባር ድረስ ሄዶ ለመዋጋት እያሳየ ያለው ተነሳሽነት ለጥፋት ኃይሎች ጭንቀት ሆኖባቸዋል።

እንደ ኮሎኔል ጌትነት ገለጻ ለጥፋት የተነሳው የህወሓት የሽብር ቡድን ገበሬ ምሁር አይልም፤ ሁሉንም እያጠፋ ነው፤ በተለይም ገበሬውን አጥፍቶ ታይቷል፤ በመሆኑም በየትኛውም ዘርፍ ያለ ሰው የሚዘምተው ለህልውናው ነው ብለዋል።