ግንቦት 11/2013(ዋልታ) – ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያውያን የሚገነባ በመሆኑ ምንም ኃይል ሊያቆመው አይችልም ሲሉ አዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል ግብጽና ሱዳን ባለሙያዎችን እንዲሰይሙ ያቀረበችውን ጥሪ ሁለቱ አገሮች አለመቀበላቸው ይታወሳል።
ግብጽ አሁንም ቢሆን የአባይን ውሃ በጋራ መጠቀም በሚለው ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ባመስማማት ሁሉን አቀፍ ስምምነት መደረግ አለበት በማለት ስትከራከር ቆይታለች።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ በመጠቀም ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ የተለያዩ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በመጠቀም ሃይል ለማመንጨት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ እነዚሁ አካላት ሳይታከቱ እየሰሩ መሆኑን የፍልስፍና ምሁሩ ዮናስ ዘውዴ /እጩ ዶክተር/ ተናግረዋል፡፡
ግድቡ በኢትዮጵያውያን የሚገነባ የኢትዮጵያውያን ሐብት በመሆኑ ምንም ኃይል ግንባታውን እውን ከማድረግ ሊያስቆመው አይቻለውም ብለዋል።
ምዕራባውያኑ የህዳሴውን ግድብ አስታከው በአገሪቱ ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ ለማሳደር እየሰሩ መሆኑን ፖለቲከኛና ፀሃፊ አንዳርጋቸው ጽጌ ተናግረዋል፡፡
ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድቡን ሙሌት በምንም መንገድ ማስቀረት እንደማይችሉም ተናግረዋል፡፡
በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም ድምፃቸውን ማሰማት ከቻሉ ግድቡን ተከትሎ የሚሰሙ ጫጫታዎችንና ጫናዎችን መቋቋም እንደሚቻልም የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ተናግረዋል፡፡
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአቋም ልዩነት ሊኖራቸው እንደማይገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የግድቡ ውሃ አሞላል ከድርድሩ ማብቃት በኋላ ይከናወን የሚባል ከሆነ አገሪቱን “በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር ያሳጣታል” በማለት የውሃ ሙሌቱን ማዘግየት እንደማይቻል መናገራቸው ይታወሳል።