ሚያዝያ 19/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ ህገወጥ ተግባራትን የፈፀሙ ከ200 በላይ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱን የከተማ አስተዳደሩ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ቦርድ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባደረገው ክትትል ሠራተኞቹ በርካታ የአሰራር ጉድለቶችን መፈፀማቸውን አረጋግጧል።
በዚህም ተገልጋይን በአግባቡ አለማስተናገድን ጨምሮ እስከ ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት የተመዘገበባቸው ሠራተኞች መገኘታቸውን ነው የገለጹት።
“በእያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ የማህበራቱ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ሠራተኛ ጉድለት አይፈፅምም ማለት አንችልም” ሲሉም ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት፡፡
በመሆኑም በየጊዜው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸው በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ጉድለት በፈፀሙ ከ200 በላይ ሠራተኞች ላይ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ 14 ዓመት የሚደርስ የእስራት እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች ከፈፀሟቸው ስህተቶች ደንበኛን አለማክበር፣ ሱቅ ዘግቶ መጥፋት፣ ምርትን ባልተገባ መንገድ ለመሸጥ ሲያወጡ እጅ ከፍንጅ መያዝ እና የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሂሳብ ማጉደል ይገኙበታል።
በዚህ ዓመት ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ዓላማውም ሌሎች ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ ለማስተማር ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 148 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሲኖሩ ማህበራቱ ከ640 በላይ ሱቆች፣ 205 የመዝናኛ ማዕከላትና ከ220 በላይ ስጋ ቤቶች ሲኖሯቸው ለበርካቶች የስራ እድል ፈጥረዋል፡