ህገወጥ የመሬት ወረራ በፈፀሙ መቶ ሀያ የስራ ኃላፊዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

ጥቅምት 05/2014(ዋልታ) ህገወጥ የመሬት ወረራ በፈፀሙ መቶ ሀያ የስራ ኃላፊዎች  ላይ ክስ መመስረቱን የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር አስታወቀ ፡፡

ለአርሶ አደሮች ከተላለፉት ሁለት ሺህ 170 ካርታዎች ውስጥ 497 የሚሆኑት ካርታዎች በህገወጥ መንገድ የተላፉና  በሄክታር 20 ነጥብ 7 የሚሆን መሬት በህገወጥ ለማይመለከታቸው ተላልፎ መገኘቱን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል ፡፡

በ252 የአረንጓዴ ቦታዎች ላይ የማጣራት ስራ መሰራቱን የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ 35 ቦታዎች  በህገውጥ መንገድ በግለሰቦች ተይዘው እንደተገኙ የገልፁ ሲሆን በህገውጥ መንገድ የተያዘ ከ100 በላይ ሄክታር መሬት ወደ መሬት  ባንክ መግባቱን  ተናግረዋል ።

በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ የተካሄደው በምርጫ 1997 እና በ2002 በመሆኑ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ይህ እንዳይደገም ጠንካራ ስራ እንደተሰራና ህገ ወጦችን መከላከል መቻሉን አስረድተዋል።

ከፍተኛ የሆነ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ የተካሄደባቸው  አቃቂ፣ ቦሌ፣ የካ፣ ለሚ ኩራና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች  መሆናቸውንም አቶ ጥራቱ  አብራርተዋል ።

በከተማዋ ካለው ሰፊ የመሬት ፍላጎት የተነሳ በህገወጥ መንገድ የመያዝ እድል ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ ከለውጡ በፊት አርሶ አደሮችን በማፈናቀል በህገ ወጥ መንገድ መሬት የሚወሰድበት ጊዜ እንደ ነበር በማንሳት  ይህም ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ዳርጐናል ብለዋል ።

የከተማ አስተዳደሩ ከባለፈው ዓመት ወዲህ በመዲናዋ በህገወጥ የመሬት ወረራና መሬት ነክ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ የአሰራር ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስኪያጁ  ተናግረዋል።

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተገን አድርገው ህገወጥ የመሬት ወረራ እንዳይፈጸም ከፍተኛ ስራ መሰራቱን ያነሱት አቶ ጥራቱ ህገ ወጥ ካርታ ተሰርቶላቸው ሊተላለፉ የነበሩ አንድ ሺህ 502 የሚሆኑ ቦታዎች ይዞታዎችን ማምከን መቻሉን አብራርተዋል ፡፡

ህገወጥ የመሬት ወረራ  ለመቅረፍ የከተማዋን መሬት በፕላን መምራት እንደሚገባ ታምኖበት እየተሰራ መሆኑን አቶ ጥራቱ  ተናግረዋል።

በመሬት ወረራ የተሳተፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የአርሶ አደር ኮሚቴዎችና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተውስዷል ብለዋል።

በአመለወርቅ መኳንንት