ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ

ሰኔ 24/2013 (ዋልታ) – በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ የጦር መሳሪያ መያዙን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አስታወቀ።

የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3-12568 አ/አ የሆነ አይሱዚ የጭነት መኪና መነሻውን ባህርዳር ከተማ ልዩ ቦታው ቀበሌ 04 በማድረግ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመጫን ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ በማድረግ በተለምዶ  ጎጃም  ኬላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደደረሰ በፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ፀረ-ኮንትሮባንድ አባሎች ከህብረተሰቡ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት መኪናውን ሲፈትሹ 88 ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦችና ከ5 ሺህ በላይ የተለያዩ ጥይቶችን ከመኪናው የላይኛው አካል ላይ ማግኘታቸውን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከዚሁ የወንጀል ድርጊት ጋር በተገናኘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በስፋት እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡