መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) መነሻውን ሰሜን ሸዋ ደራ ያደረገው አይሱዚ ተሸከርካሪ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ጥይቶችን ይዞ ሲንቀሳቀስ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት በጋራ ባደረጉት ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተሽከርካሪው በቁጥጥር ስር የዋለው መጋቢት 27/2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ፅዮን ሆቴል ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት አካባቢ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ከኅብረተሰቡ የተገኘውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ባደረጉት ክትትል ኮድ 3 አ/አ 49819 የሆነ አይሱዚ ተሸከርካሪ አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ሥር ሲውል በተለያዩ ማዳበሪያዎች የተጫኑ 6042 የብሬን እና 7800 የክላሽ በአጠቃላይ 13 ሺሕ 842 ጥይት በተሸከርካሪው የውስጥ አካል ተሸሽገው እንደነበረ ፖሊስ አስታወቋል፡፡
በዕለቱ በእግዚቢት ከተያዙት ጥይቶች ጋር አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ አመልክቷል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW