ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለሚንቀሳቀሰው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይል ሽኝት ተደረገለት

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይል

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የጁንታውን ቡድን በመደምሰስ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚካሄደውን ዘመቻ ለማገዝ ለሚንቀሳቀሰው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ልዩ ሃይል በዛሬው ዕለት ሽኝት ተደርጎለታል።

የጁንታው ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ሀገር የመበታተን ተግባር ሙሉ በሙሉ በማክሸፍ የህዝቦችን አንድነት መመለስ የልዩ ሃይሉ ዓላማ መሆኑን የክልሉን ፕሬዝዳንት በመወከል አቶ ቢኒያም መንገሻ ተናግረዋል።

በፖለቲካው መድረክ ሽንፈትን የተከናነበው ይህ ስግብግብ ጁንታ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀበራቸው የተንኮል ፈንጅዎች ችግር የፈጠሩ ቢሆንም፤ በሰላም ወዳዱ ህዝብና በሰራዊቱ ከፍተኛ ጥረት ሃሳቡ እንዳይሳካ ተደርጓል ብለዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው፣ ይህ አጥፊ ቡድን ከውጭ የሀገራችን ጠላቶች ጋር በመቀናጀት የፈጸመው እኩይ ተግባር የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርገው ነው በማለት ቡድኑን ለመደምሰስ አደራ የተሰጣቸው የልዩ ሃይል አባላት በድል አድራጊነት እንደሚመለሱ ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ኮማንድ ፖስትን በመወከል ንግግር ያደረጉት ኮሎኔል ፋሲል ይግዛው በበኩላቸው የልዩ ሃይሉ አባላት በህወሓት ጠንሳሽነት በዞኑ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ የከፈሉት መስዋዕትነት የጀግንነታቸው ማሳያ ነው ብለው አሁንም በሰሜኑ ግንባር ተገኝተው ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ይህን አኩሪ ገድል መፈጸም እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።