ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን የካፋ ዞን እናቶች ገለጹ

ሐምሌ 19/2013 (ዋልታ) – ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በ300 ሺህ ብር የሚገመት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን የካፋ ዞን እናቶች ገለጹ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሀገሪቱን ሰላም በማደፍረሱና ህጻናትን ወደ ጦርነት ማሰማራቱ እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል፡፡

እናቶቹ ከቀደምት ሴት ጀግኖች የተማሩትን ወኔ በመሰነቅ በከሃዲው የህወሓት ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከማድረግ ባለፈ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን ህጻናትን ለጦርነት በማሰማራት እየፈጸመባቸው ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያወግዙት ገልጸው፣ የዞኑ ሴቶች ለመከላከያ ሰራዊት ዳቦ ቆሎ፣ በሶ እና  የተለያዩ ምግቦች ያዘጋጁ ሲሆን፣ በቀጣይም ሀገራዊ ግዴታቸውን በተለያዩ መንገዶች እንደሚወጡ ጠቁመዋል።

የካፋ ዞን ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት መንገሻ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ህጻናትን ከትምህርት ገበታቸው ነጥሎ በለጋ እድሜያቸው ለጦርነት ማሰማራቱ እንዳሳዛናቸው ገልጸዋል።

ይህንን አሳፋሪ ድርጊት ከማውገዝ በተጨማሪ የዞኑ ሴቶች በዓይነትና በገንዘብ እንዲሁም ስንቅ ለኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚያደርጉት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው፣ ሀገር በእናት እንደሚሰየም ሁሉ እናቶች ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጡ ገልጸው፣ በአሸባሪው ህወሃት የተቃጣውን ትንኮሳና ጥቃት ለመመከት ለሀገር አንድነት ውድ ሕይወቱን እየከፈለ ካለው መከላከያ ሠራዊት ጎን የዞኑ ሴቶች በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል፡፡

የሀገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም የጋራ አስተሳሰብ እና አንድነት ሊኖረው እንደሚገባና ሴቶች በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ ህይወት ገልጸዋል።

አሸባሪው ሕጻናትን ለትምህርት እንጂ ለጦርነት በመመልመል የፈጸመው ወንጀል የአሸባሪነቱን ጥግ የሚያሳይ መሆኑንም ነው ያሰረዱት።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሀገሪቱ ሰላም ለማደፍረስና ልማት ለማደናቀፍ ከውጭ ኃይላት ጋር እየሰራ ያለው ተግባር አሳፋሪ በመሆኑ መንግስት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ለማጠናከር ለመከላከያው ሰራዊት የሚሆን ስንቅ በዞኑ ሴቶች እየተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል።

የተዘጋጀው  ስንቅ በነገው ዕለት ለሠራዊቱ እንደሚላክም ከካፋ ዞን መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።