ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስፖርታዊ ውድድር ሊካሄድ ነው

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስፖርታዊ ውድድሮች ሊካሄዱ መሆኑን የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ብሄራዊ የስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ።
የውድድሩን ዓላማ በማስመልከት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታና የአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ብሄራዊ የስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ መግለጫ ሰተዋል።
በመግለጫቸውም አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል በአማራና አፋር ክልሎች የከፈተውን ጦርነት የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በመመከት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለዚህም በብሄራዊ ደረጃ የኪነጥበብና ሚዲያ ኮሜቴ ስር የተዋቀረው ብሄራዊ የስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ባለፉት ሳምንታት ለመከላከያ ሰራዊት በሚደረጉ ድጋፎች ዙሪያ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
“ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፣ የትም፣ መቼም፣ በምንም” እና “የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ”! በሚል መሪ ሃሳብ በስፖርት ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ታስቦ ወደ ተግባር ተገብቷልም ነው ያሉት።
በመርሃ ገብሩ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማዘጋጀት ህብረተሰቡ ከሀገር መከላከያ ስራዊት ጎን መቆሙን ለማሳየት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ከስፖርታዊ መድረኮች ጎን ለጎንም የደም ልገሳ የሚካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ዙር የማስ ስፖርት ህዝባዊ ንቅናቄ በነገው እለት (ነሀሴ 9 ቀን 2013 ዓ.ም) በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ይካሄዳል ብለዋል።
በሁለተኛ ዙር የ5 ኪሎ ሜትር ህዝባዊ የጎዳና ሩጫ ነሀሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ በሶስተኛ ዙር ደግሞ ነሀሴ 23ቀን 2013 ዓ.ም የጎዳና ላይ የእግር ጉዞና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱም ነው አቶ ሀብታሙ ያስታወቁት።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በአጠቃላይ በሶስቱም ዙሮች ከ900 ሺህ በላይ ሰዎች በስፖርቱ ህዝባዊ ንቅናቄ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ከስፖርት ውድድሮች በተጨማሪ ለሰራዊቱ የገቢ ማሰባሰብ “በሁሉም ክልሎች ይካሄዳል፤ የደም ልገሳም ይከናወናል” ነው ያሉት የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ።
የኢትዮጵያ ቮሊ ቦል ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የደም ልገሳ እና ገቢ የሚያሰባስቡ መሆኑም ታውቋል።
የብሄራዊ ስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ ባለድርሻ አካላት ተልዕኮውን ወስደው ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ላደረጉት ጥረትም ምስጋና አቅርበዋል።