ለሀገር ዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በወላይታ ዞን የትግራይ ተወላጆች ገለጹ

ጥቅምት 5/2015 (ዋልታ) ለሀገር ዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ በወላይታ ዞን የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

በዞኑ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ህዝብ የሚያደርሰውን ጥቃት ሊያቆም ይገባል የሚል የተቃውሞ ሰልፍ በሶዶ ከተማ አካሂደዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አክሊሉ ለማ አሸባሪው ህወሓት በትግራይ ህዝብ እራሱን በመከለል የሀገሪቱን ሰላም በማደፍረስ ላይ እንዳለ ገልጸዋል።

መንግስት የጥፋት ኃይሉ በትግራይ፣ በአማራና በአካባቢዎቹ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በሚያደርገው የሰላም ግንባታ ሂደት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰልፉ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እኛ ከሌሎች ኢትዮጵያዊን ጋር በደም የተሳሰርን የአንድ ሀገር ልጆች ነን፤ ነገር ግን ህወሓት የከፈተው ጦርነት የትኛውንም የትግራይ ህዝብ የማይወክል ነው፤ የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊ ነው ብለዋል።

ትግራይ ያሉ ቤተሰቦቻችንን በሰላም እጦት ይኑሩ ይሙቱ የምናውቀው ነገር የለም ያሉት ተሣታፊዎቹ የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት በሚያደርገው ርብርብ የበኩላቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን የላከልን መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW