ለሁሉም ልጆች የምትመች አዲስ አበባን እንገነባለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ነሐሴ 15/2014 (ዋልታ) ለሁሉም ልጆች የምትመች አዲስ አበባን እንገነባለን ሲሉ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት እንደገለፁት ትውልድ ለም መሬት ነው፣ መልካም ነገር ከዘራንበት መልሶ የሚከፍልና ፍሬውን በእጥፍ የምናጭድበት ነውም ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም በነገዋ ኢትዮጵያ መፃኢ እድል ላይ ዘር ዘሪው ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡

በዛሬው እለት የከተማ አስተዳደራችን አስውቦ ባስገነባው የ1.4 ኪ.ሜ ከወሎ ሰፈር- ኡራኤል መንገድ ላይ በእሁድ ቀን ከመኪና ነፃ የህፃናት አካላዊ እንቅስቃሴና የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆን ወስነን እንቅስቃሴውን አስጀምረናልም ብለዋል።

እንቅስቃሴው በቅርቡ በተሟላ ሁኔታ ወደ ተግባር ከገባንበት የቀዳማይ ልጅነት እድገትና እንክብካቤ ፕሮግራም ማዕቀፍ አንዱ ነው ያሉት ከንቲባዋ በዚህ ፕሮግራም የሚሳተፉ ልጆች ቤተሰቦች ገቢ ይኑራቸው፤ ገቢ አይኑራቸው በጎዳና ላይ የሚኖሩ፤ ቤት ያላቸው፣ የሌላቸው በአጠቃላይ አዲስ አበባ ለሁሉም ልጆች ምቹ የሆነች እንድትሆን እንሰራለን ብለዋል።

ፕሮግራሙን ቤተሰብ ድረስ ለማውረድ 5 ሺሕ ባለሙያዎች በመቅጠር ወደ ሁሉም የከተማዋ አካባቢ የምናሰማራ ይሆናል ሲሉም ከንቲባዋ አመላክተዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!