ሐምሌ 18/2013 (ዋልታ) – ለሃገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍና አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃረሪ ክልል እናቶች ገለጹ።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አዲስ አለም በዛብህ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱጀባር መሀመድና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በየወረዳው እናቶች ለሰራዊቱ የሚያደርጉትን የስንቅ ዝግጅት አበረታተዋል።
በስንቅ ዝግጅቱ ከተሳተፉት መካከል የሀኪም ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ኢፍቱ ተስፋዬ እንዳሉት በወረዳው የምንገኝ እናቶችና ሴቶች በግዳጅ ላይ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚሆን በሶ፣ ዳቦ ቆሎ እና ሌሎች ስንቆችን እያዘጋጁ ይገኛሉ።
ዝግጅቱም በየአካባቢው የሚገኙ ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እና መዋጮ የተዘጋጀ መሆኑን በመጠቆም “በተለይም ሴቶች ለሀገር ህልውና እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት የኋላ ደጀን መሆን ይጠበቃል” ብለዋል፡፡
ሌላዋ የቀበሌ 17 ነዋሪ እናት መስከረም በበኩላቸው “ለህይወቱ ሳይሳሳ ለሀገር ሉአላዊነት እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የክልሎቹ የጸጥታ አካላት ስንቅ እያዘጋጀን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“የሰራዊቱ አባላትም እኛ እናቶቻቸው እና እህቶቻቸው ከጎናቸው መሆናችንን እንዲረዱልን መልዕክቴን አስተላልፋለሁ” ያሉት ወይዘሮ መስከረም “ህዝቡም ለሀገር ደጅን ለሆነው ሰራዊት ድጋፉን ማጠናከር ይገባዋል” ብለዋል።
በጂኔላ ወረዳ በስንቅ ዝግጅት ሲሳተፉ ያገኘናቸው ሌላዋ እናት ወይዘሮ ባዩሽ ጌታቸው በበኩላቸው እንዳሉት መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ በራስ ተነሳሽነት በተካሄደው የስንቅ ዝግጅት ላይ በመሳተፋቸው ከፍተኛ ኩራት ተሰምቷቸዋል።
በቀጣይም በገንዘብ በጉልበትና በሌሎችም ድጋፎች ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
“በወረዳው የምንገኝ ሴቶች በነቂስ በመውጣትና ስንቅ በማዘጋጀት ለሀገሩ መስዋዕት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አጋርነታችንን እያሳየን እንገኛለን” ያሉት ደግሞ ሌላዋ የጂኔላ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ እጸገነት ውቤ ናቸው፡፡
ከስንቅ ዝግጅት ባለፈም ለሰራዊቱ ደም በመለገስ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ድጋፋችንን ከማጠናከር ባለፈ እስከ ግንባር ድርስ በመሄድ ለሰራዊቱ ስንቅ የማቀበልና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
መላው ህዝብም ለሰራዊቱ በሚችለው ሁሉ መደገፍ ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ አዲስ አለም በዛብህ ለሀገር ሲል እየተዋደቀ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተደረገ ያለውን የስንቅ ዝግጅት አድንቀዋል፡፡
በቀጣይም በደም ልገሳ እና በገንዘብ እየተደረጉ ያሉ ድጋፎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው፣ “እኛ ሴቶች ከጥንት ጀምሮ በሀገርጉዳይ ላይ በስንቅ ዝግጅትና በግንባር በመሰለፍ ቀዳሚዎች ነን” ብለዋል።
እየተደረገ ያለው የስንቅ ዝግጅትም የቀድሞውን ታሪክ የደገመ ነው” ያሉት ወይዘሮ ሚስራ “በቀጣይ የሀገር ደህንነት ተጠብቆ እንዲቆይ ድጋፎችና እየተከናወኑ ያሉ ሌሎች ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡