ለህዳሴ ግድቡ በ48 ሰዓታት ከዳያስፖራው 70 ሺህ ዶላር ተሰበሰበ


ሐምሌ 19/2013 (ዋልታ) –
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ የሚደረግበት ድረ ገፅ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ከ583 ዳያስፓራዎች 70 ሺህ 380 ዶላር መሰብሰቡ ተገለፀ፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጰያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች www.mygerd.com የሚል ድረ ገጽ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ 70 ሺህ 380 ዶላር ድጋፍ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ድረ ገፁ በተከፈተ 48 ሰዓታት ውስጥ 583 ለጋሾች ለህዳሴ ግድቡ 70 ሺህ 380 ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ድረ ገጹ የፈለጉትን መጠን ማስገባት እንዲችሉ ክፍት የሆነ ሲሆን 36 ሰዎች ግድቡን በተለያየ መንገድ እንደግፍ የሚል ዘመቻ እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የተሰበሰበው በአማካኝ በሰአት ሲታይ አንድ ሺህ 510 ዶላር ሲሆን ይህ ደግሞ ዲያስፖራው በቁጭት እየደገፈ መሆኑን ያሳያል ብለዋል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡