ጥቅምት 27/2014 (ዋልታ) በምርት ከተሸፈነው ሰብል 25 በመቶ የደረሰ ሲሆን የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጀነራል ገርማሜ ጋሮማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በምርት ዘመኑ 12 ሚሊዮን 540 ሺሕ ሄክታር መሬት በምርት መሸፈን ተችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሰብል ከተሸፈነው ውስጥ 25 በመቶ ለመሰብሰብ የደረሰ በመሆኑ በቂ ዝግጅት በማድረግ የምርት ስብሰባ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፈጥነው የተዘሩና በስምጥ ሸለቆ ያሉ ምርቶች ለመሰብሰብ የደረሱ በመሆናቸው አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ቦቆሎ፣ ጤፍና ስንዴ የደረሱ በመሆናቸው በጥሩ ሁኔታ በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰብል በደረሰባቸው አካባቢዎች ምንም አይነት የዝናብ ችግር ባለመኖሩ በተያዘው እቅድ የመሰብሰብ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ለመሰብሰብ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ደመናዎች አሉ፤ ነገር ግን ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡